What We Believe
የእምነት አንቀጽ
አዲስ ኪዳን የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን በቦስተን የጠቅላላ ጉባዔ እግዚአብሔር ሕብረት የደቡብ ኒው ኢንግላንድ ቅርንጫፍ ጉባኤ እግዚአብሔር አባል ስትሆን ለወንጌል ሥራ እንደ አስፈላጊነቱ ከሌሎችም ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው አብያተ ክርስቲያናት ጋር ሕብረት ታደርጋለች።
እኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ከዚህ ቀጥለው በተገለጹት መሠረታዊ ሐሳቦች ያለምንም ለውጥ በፍፁምና ባንድ ልብ አምነን እንቀበላለን።
- መጽሐፍ ቅዱስ፤ (በብሉይና በአዲስ ኪዳን የሚገኙት ስልሳ ስድስት መጻህፍት) ቅዱሳን ስዎች በእግዚአብሔር መንፈስ በመነዳት እንደጻፉትና ምንም ስህተት የሌለበት ስልጣን ያለው የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ እናምናለን።
- እግዚአብሔር በሦስት አካላት ዘላለማዊ በሆነ መንገድ በሚኖር አንድ አምላክ እናምናለን፤ እነዚህም አካላት አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እንደሆኑ እናምናለን።
- ኢየሱስ ክርስቶስ የሥላሴ አካል እንደሆነ፤ ከድንግል ማርያም በመወለድ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም እንዳገለገለ፤ የሰውን ልጅ ለመቤዠት ደሙን እንዳፈሰሰ፣ እንደሞተ፣ እንደተቀበረና በሦስተኛውም ቀን በአካላዊ ትንሳኤ በመነሳት በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ፤ እንዲሁም ቅዱሳንን ሊሸልምና በዓለምም ላይ ሊፈርድ በክብርና በኃይል እንደሚመጣ እናምናለን።
- መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ አካልና አምላክ እንደሆነ፤ ዓለምን ስለ ኃጢአት፤ ስለ ፍርድና ስለ ጽድቅ በመውቀስ ክርስቶስን እንደሚያከብር፤ በቅዱሳን በማደር ቅዱሳንን ለቅድስና ሕይወትና ለአገልግሎት እንደሚያዘጋጅ፤ ለቤተ ክርስቲያን መታነጽና ዕድገት መንፈሳዊ ስጦታዎችን፤ እንደወደደ እንደሚሰጥ እናምናለን።
- ድነት በክርስቶስ የመስቀል ሞትና ትንሳኤ ያለ አንዳች የሰው ጥረት በእግዚአብሔር ጸጋ እንደሚገኝ፤ ይህም ድነት በመንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ አሰራር በእምነት ብቻ እውን እንደሚሆን እናምናለን።
- በክርስቶስ ኢየሱስ ጌትነትና አዳኝነት በሚያምኑ አብያተ ክርስቲያናትና ምዕመናን መካከል በሚሆን የመንፈስ አንድነትና ኅብረት እናምናለን።